“ወላጆችም እኮ ከኮቪድ-19 ‹የአፍታ ዕረፍትን› ይሻሉ” ትላለች የሰቆቃ ሰለባዎችን የምትረዳው የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ

አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ

በ ወሰን ሙላቱ
Tigist Waltenegus is a mother of three and a well accomplished trauma psychologist who has served in this profession for the last 12 years.
UNICEF Ethiopia/2020/Mopix
03 June 2020

ትዕግሥት ዋልተንጉሥ የሦስት ልጆች እናት እና ብቃቷን ያስመሰከረች የሰቆቃ የሥነ-ልቦና [ሕክምና] ባለሙያ (trauma psychologist) ስትሆን፤ በዚህ ሙያ ላለፉት 12 ዓመታት አገልግላለች፡፡ የሰቆቃ የሥነ-ልቦና ሕክምና፤ ከአእምሮ ጤና እንክብካቤ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን፤ መፍትሔ የሚሻ የሥነ-ልቦናዊ ሰቆቃ ወይም ስቃይ የደረሰባቸውን ሰዎችን እንዲያገግሙ ለመርዳት ምክር ሰጪዎች የሚጠቀሙበት [የሕክምና ዘርፍ] ነው፡፡

“በሥራዬ ከማገኘው ሁሉ አብልጦ ሐሤት የሚሰጠኝ ነገር፤ ሰቆቃ ታሪክ ሆኖ ስመለከት ነው” ትላለች፡፡ “ሰዎች የደረሰባቸውን መርሳት አይችሉም፤ ስቃዩን ግን መተው ይችላሉ፡፡ እንዲህ ባለ ትርጉም በሚሰጥ ሥራ የሂደቱ እና የለውጡ አንድ አካል ሆኜ መገኘት አጅግ አመርቂ ነው፡፡”

በኮቪድ-19 የተነሣ፤ ትዕግሥት ባብዛኛው ሥራዋን እያከናወነች ያለችው በበይነ-መረብ (online) አማካኝነት በመሆኑ ጊዜዋን ከቤተሰቧ ጋር በመኖሪያ ቤት ውስጥ እያሳለፈች ነው፡፡

 “እኛ ወላጆች በሥራ ብዛት የተነሣ ከቤተሰቦቻችን ጋር ለመሆን ባለመቻላችን ቅሬታ ያድርብን ነበር፡፡ አሁን ምንም ዓይነት ሰበብ የለም፡፡ ይህንን ጊዜ ከቤተሰቦቻችን ጋር አብረን ለማሳለፍ፣ ለመወያየት እና ለመከራከር፣ የምናደርጋቸውን ነገሮች ለማቀድ፣ እንዲሁም የቤቱን ውስጠ-ደንብ ለመደንገግ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ሕፃን ልጆቻችንን በተመጣጠነ ምግብ ብቻ ሳይሆን በሥነልቦና-ወማኅበራዊ [psychosocial] ክብካቤ እና ድጋፍ የማሳደጊያም ጊዜ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ የሦስት ወር አራስ ልጄን ያለምንም ማቋረጥ ጡት እያጠባሁ ሲሆን፤ ይህም ጡት ለሚያጠቡ ሌሎች እናቶች ትልቅ አርአያ ነው፡፡” 

እንደ ሰብአዊ ፍጡር የሚያስጨንቅ ቢሆንም፤ ኮቪድ-19 በቤተሰባዊ ሕይወት ላይ የነበረውን መዛነፍ ለማረም እና ለማቃናት ወርቃማ ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡

 “ቫይረሱ በኢኮኖሚ የሚጎዳ፤ በዚያም ላይ ሰዎች ለማኅበራዊ ኑሮ የሚሰጡትን ዋጋ ስናስበው ደግሞ ማኅበራዊ ርቀት [social distancing] የሚያስጨንቅ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይሁንና የጊዜ ስጦታን አበርክቶልናል፡፡”

ትምህርት ቤቶች የተዘጉ እንደመሆኑ፤ አብዛኞቹ ሰዎች ሕፃናት ከትምህርታቸው ብቻ እንደተስተጓጎሉ አድርገው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ የታሪኩን ሙሉ ገጽታ አያሳይም፡፡ [ሕፃናት] ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወትን ጨምሮ ማኅበራዊ ሕይወትንም ነስቷቸዋል፡፡

ትዕግሥት እንደምትለው፤ በዚህ ወቅት በውጥረት፣ በድብታ (depression)፣ እና በፀባይ መቀያየር የተነሣ ከደረሰባቸው የስሜት መናወጥ ጋር የሚታገሉ፤ እናም ከሕፃን ልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት እንደሚመሩ ችግር የገጠማቸው ወላጆች አሉ፡፡

 “አንዳንዴምክርን በብርቱ ከሚሹ ወላጆች ስልክ ይደወልልኛል፡፡ ሕፃን ልጆቻቸው ማድረግ የሌለባቸውን ነገር በተደጋጋሚ ነግረዋቸው እንኳ [ትዕዛዛቸውን] እየተቀበሏቸው እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ’ተው ተይ ተው ተይ’ ማለትም ይሄንን ወይንም ያንን ማድረግ አቁም/አቁሚ እያልን ደጋግመን አንናገራለን፤ እናም [ድግግሞሹ] እያለ ይቀጥላል፡፡” 

እንደነዚህ መሰል ሁኔታዎች ሲፈጠሩ፤ ወላጆች “የአፍታ ዕረፍት” ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ታምናለች፡፡

“አካላዊ ሁኔታቸውን ማጤን እና [ሕፃናት ከያዙት ነገር ላይ አትኩሮታቸውን] የሚያስቀይስ ብልኃትን መጠቀም ሊረዳ እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ ትክት ብሏቸው ከሆነም፤ ነገሩን እንዳልተፈጠረ ሊያጣጥሉት እና ሁሌም ነገሮችን በቁጥጥራቸው ሥር እንዳደረጉ ማሰብ አይገባቸውም፡፡ ሕፃን ልጆቻቸውን እንዳፈቀዳቸው የመምታት እና በእነርሱ ላይ የመጮህ  መብት ያላቸው አድርገው ሊገምቱ አይገባም፡፡ ራሳቸውን ካረጋጉ እና ቀልባቸውን ከመለሱ በኋላ ግን፤ ነገሩን [ምናልባት] በሌላ አቅጣጫ ሊገመግሙት እና ሕፃን ልጆቻቸውንም ሳይጎዱ ነገሩን ለማሳለፍ ይችሉ ይሆናል፡፡

 “አንዳንዴ እንደ ዳይኖሰር የገዘፈ ፍጡር፤ እንደ ጉንዳን ባነሰ ፍጡር ላይ ቁልቁል እየተመለከተ እንደሚያንባርቀው ዓይነት ሆኖ ይሰማል፡፡ የእኛ አካላዊ ቁመና እና ድምጽ ወትሮም ቢሆን ለሕፃናት ኅሊና እጅግ የገዘፈ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ራሳችንን ካልገራን፤ [ሕፃናትን] ወደ ጸብ እንዲገቡ፣ እንዲኮበልሉ፣ አሊያም [አካላቸው በድንጋጤ] ድንገት በድን የሚሆንበትን ክስተት ልንፈጥር እንችላለን::

“በሌላ በኩል፤ ሕፃናት የቤተሰቦቻቸውን ፈለግ እንደሚከተሉ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ሕፃናት የወላጆቻቸው ነፀብራቅ እና አብዛኛውን ጊዜ የሚያዩትን አስመስለው የሚተገብሩ ናቸው፡፡ ይህንን እና ያንን አድረጉ እያሉ በተደጋጋሚ ከመንገር፤ ወላጆች ራሳቸው በማድረግ በምሳሌ ሊመሯቸው ይገባል፡፡

እጅግ በርካታ የጥቃት ክስተቶችን እንደታዘበ የሰቆቃ የሥነ-ልቦና ሕክምና ባለሙያነቷ፤ በዚህ ወቅት ያለው የሕፃናት ደኅንነት አጠባበቅ ጉዳይ ትዕግሥትን ያሳስባታል፡፡

 “በቤት ውስጥም ሆነ በውጪ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ለተጋለጡ ሕፃናት የሚደረገው የደኅንነት አጠባበቅ ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ የጥቃቶቹ መነሾዎች የኢኮኖሚ ጫና የፈጠረው ከሆነ፤ የገንዘብ ድጋፍ ሲገኝ [ጥቃቶቹ] ሊገቱ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ለእኔ ከሁሉም የላቀ ትኩረት የሚሻው እና እጅግ የከፋው የጥቃት ዓይነት የወሲብ ጥቃት ነው፡፡

“አባቶችን ጨምሮ በቅርብ የቤተሰብ አባላት አማካኝነት በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ በርካታ የወሲብ በደል ድርጊቶች አጋጥመውኛል፡፡ ከዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ እና ከቦታ ጥበት የተነሣ፤ መላው ቤተሰብ በአንድ ላይ ለመተኛት የሚገደዱበት ሁኔታ ደግሞ ነገሩን ያከፋዋል፡፡ ስለጉዳዩ ዝምታን የሚመርጡ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ቀሪዎቹን ሕፃናት ለመታደግ፣ ትዳራቸውን ለማቆየት፣ አሊያም የኢኮኖሚ ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ትልቋ ሴት ልጃቸው በአባትየው በደል እንዲደርስባት አሳልፈው የሚሰጡ እናቶች አጋጥመውኛል፡፡ ነገር ግን የእነዚህን ሕፃናት ደኅንነት የምናስጠብቅበትን፤ ብሎም ደኅንነት የሰፈነበት ቦታ እና መጠለያ የሚሟላበትን መንገድ ማግኘት አለብን፡፡”

ትዕግሥት እንደምትለው ሰዎች በዚህ ወቅት በድብታ ከተጠቁ፤ በበይነ-መረብ እንደሚሰጠው ዓይነት የምክር አገልግሎትን የመሳሰሉ ዘመናዊ አማራጮችን ብቻ ሳይሆን፤ ከችግራቸው ለመላቀቅ የሚያግዛቸውን ከሃይማኖት አባት ጋር እንደመወያየት ያሉ ዘልማዳዊ (traditional) አማራጮችንም ጭምር ለመጠቀም ይችላሉ፡፡

ትዕግሥት ለወላጆች እና ለተንከባካቢዎች የሚከተሉትን ምክሮች ትጠቁማለች፡-

1. ሕይወትን በተለመደው› ሁኔታ ለማስቀጠል አዲስ የቤት ውስጥ “የሠርክ ሥራ እና ልማድ”ን ያስለምዱ፡- እንደ አንድ የሰቆቃ የሥነ-ልቦና ሕክምና ባለሙያ፤ ሰቆቃ የደረሰባቸው ሰዎች ዕለት-ተዕለት መላልሰው/ደጋግመው የሚከውኑት/የሚጠመዱበት የሠርክ ሥራ (routine) እንዲሁም ልማድ/ዘይቤ (ritual) እንደሌላቸው መታዘቧን ትዕግሥት ትናገራለች፡፡ በመሆኑም ቀኑን የሚሞላ ሥራን፤ እንዲሁም የሕይወት ፍሰት እንደተለመደው እየቀጠለ እንደሆነ ስሜት ለማሳደር እንዲቻል ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ የሚያከናውነውን ልማድ/ዘይቤ መፍጠር/ማስለመድ ያሻቸዋል፡፡

2. ስለ ኮሮና ቫይረስ ለሕፃናት ለማስተማር ተረት ማውጋት እጅግ ተመራጩ ዘዴ ነው፡- እንደ “ቫይረስ” እና “ጭንብል” የመሳሰሉ ቃላትን በተለይ ለትንንሽ ሕፃናት ለማብራራት ሊያዳግት ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ/ዲት ልጅ ላይ ያጠነጠነ በሰውኛ የተዋዛ ተረት ግን ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡ በጭራቅ እና በምትሃት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ተረቶችን ለመተረክ ከቻሉ፤ በእጅ መታጠብ ዙሪያ ተረት መፍጠር ሊሳንዎ አይገባም፡፡ ለትልልቅ ሕፃናት ደግሞ ከህልማቸው እና ከመጻኢ ዕድላቸው ጋር ማቆራኘት ይችላሉ፡፡ (የአርታኢው ማስታወሻ፡ ለሕፃን ልጆችዎ ስለ ኮቪድ-19 እንዴት ማብራራት እንደሚችሉ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ይህንን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ  የኔ ጀግና መጽሀፍ፡ ህጻናት ኮቪድ-19ን እንዴት አድርገው እንደሚያሸንፉት ለማሳየት ተብሎ የተዘጋጀ ነው፡፡)

3. ሕፃናትን በጥሞና ያድምጡ፡- በብዙ ዘልማዳዊ ኅብረተሰቦች ውስጥ፤ ሕፃናት በቤት ውስጥ ካሉት [ግዑዝ] የመገልገያ ዕቃዎች መካከል አንደ አንዱ የሚታዩ  ናቸው፤ [በዚህ ዕሳቤ] ዋጋ አላቸው፡፡ ሆኖም በወሬ ለመሳተፍ እና አስተያየታቸውን ለመስጠት አይፈቀድላቸውም፡፡ ሕፃን ልጆችዎን ሲያነጋግሩዎቸው በዝምታ ጣራ ጣራውን የሚመለከቱ ከሆነ ሊያሳስብዎ ይገባል፡፡ የዚህም ምክንያት ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ አመኔታን ባለመፍጠርዎ እና [አካላዊ] የፊት-ለፊት ውይይትን ባለማስለመድዎ ስለሆነ ሕፃን ልጆችዎ ከእርስዎ ጋር እንዴት እንደሚያወሩ ለማወቅ ይቸግራቸዋል፡፡

4. መዳበስ ፈዋሽ ነው፡- ሕፃን ልጆችዎን በማቀፍ አፍቅሮትን ይለግሷቸው፡፡

5. የትንፋሽ አሳሳብ ልምምዶች (breathing exercises) ሕፃናትን እንዲረጋጉ ያግዟቸዋል፡- [ልምምዶቹ] ሕፃናት ስሜታቸውን መግራት አንዲለማመዱ የሚያግዛቸው እና ወደ ጎልማሳ የዕድሜ ደረጃ ሲሸጋገሩም የሚጠቅሟቸው ናቸው፡፡ 

6. የሕፃን ልጆችዎን አካላዊ ቋንቋ ያስተውሉ፡- ሕፃናት ውጥረት ውስጥ ሲገቡ፤ ለእርስዎ በአንደበታቸው አይነግሩዎትም፤ ግን [በሌላ አኳኋን] ያሳዩዎታል፡፡ ከውካዋ (hyperactive)፣ ዝምተኛ፣ ቀባጣሪ፣ አልቃሻ/ብስክስክ ሊሆኑ፤ ወይም ሌሎች ስሜቶችን ሊያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ አካላዊ ቋንቋቸውን መገንዘብ፤ እና ምን እንዳጋጠማቸው መመርመር ይገባዎታል፡፡

7. የቤቱን ውስጠ-ደንብ በመደንገግ ሂደት ውስጥ ሕፃናትን ያሳትፏቸው፡- ኮቪድ-19 የቤቱን ውስጠ-ደንብ በጋራ ተወያይቶ ለመደንገግ አጋጣሚውን ሰጥቶናል፡፡ ሕፃናት በውይይቶቹ ውስጥ ተሳትፈው እና ፈቃደኝነታቸውን ሰጥተው የነበረ ከሆነ፤ አስቀድመው በመስማማታቸው የተነሣ፤ የሚጣልባቸውን ቅጣት እንኳ በይሁንታ ይቀበሉታል፡፡

8. ጨዋታ የሕፃናት ሕይወት ትልቁ አካል ነው፡- ከሕፃን ልጆችዎ ጋር ለመጫወት በየዕለቱ ቢያንስ 30 ደቂቃ ይመድቡ፡፡

10. የልጅ አስተዳደግ ዘዴን እንደ ሕፃናቱ የዕድሜ ደረጃ አብሮ መቀየር የግድ ይላል፡- የሰባት ዓመት ዕድሜ ያለውን/ላትን እና የ14 ዓመት ዕድሜ ያለውን/ላትን በተመሳሳይ አኳኋን መቅረብ አይቻልዎትም፡፡ በዐሥርዮ ዕድሜ (teenagers) ውስጥ (ከ13 እስከ 19 ዓመት) ያሉት፤ ነገሮችን በራሳቸው ውሳኔ እንዲያካሂዱ ዕድል ሊሰጧቸው ይገባል፡፡ እንደየፍላጎታቸው የሚሠሩትን ነገሮች ሊያዘጋጁላቸው የሚገባ ሲሆን፤ በዕድሜ ላነሱት ሕፃን ልጆችዎ ደግሞ እንደ ቡድን መሪ እንዲሆኗቸው ላቅ ያሉ ኃላፊነቶችን ይስጧቸው፡፡ በዚህ [የዕድሜያቸው] ምዕራፍ ላይ መሪ እንጂ ጭፍራ/ተከታይ መሆንን አይሹም፡፡ የግለ-ሚሥጥር (privacy) መብታቸውን ሊያከብሩላቸው እና ቁጥጥርዎን በትልልቁ ነገር ላይ እያደረጉ [በዙሪያቸው የሚካሄደውን] እንዲመራመሩ ይተዉአቸው፡፡ (የአርታኢው ማስታወሻ፡ ለበለጠ መረጃ የልጅ አስተዳደግ በኮቪድ-19 ወቅት የሚለውን ይመልከቱ፡፡)

ተጫዋች እና ሩህሩህ የሆነችው ትዕግሥት፤ በኮቪድ-19 ወቅት በሰዎች ይልቁንም በሴቶች እና በሕፃናት ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ በመፍጠር ረገድ፤ እሷ እና የሥነ-ልቦና ሙያ ዐቻዎቿ የሚያካሂዱት ሥራ ሊያበረክት የሚችለው አቅም የትዕግሥትን መንፈስ አነቃቅቶታል፡፡

“አስታውሳለሁ የሥነልቦና ባለሙያ ሆኜ ሥራ ስጀምር እና ሦስት ሆነን ቢሮ ስንከፍት፤ ሰዎች በእኛ ይሳለቁብን እና እንዲያውም እንደ መዳፍ አንባቢ ይቆጥሩን ነበር፡፡ የሬድዮ ፕሮግራም ከጀመርን በኋላ ነው ሰዎች ስለሥራችን ተረድተው ገጠመኞቻቸውን ለእኛ ለመንገር እና ምክር ለመጠየቅ ይበልጥ ፈቃደኛ መሆን የጀመሩት፡፡ አሁን ላይ እገዛ ፈልገው ያለጎትጓች በራሳቸው ጊዜ የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞች እንዳፈራን ስናገር ያኮራኛል፡፡ በደንበኛ ብዛት ብንጥለቀለቅም በበጎ የሚታይ ነው” በማለት ታክላለች፡፡