በኮሮና ሻይረስ ወረርሽኝ ላይ የተደረበው የበርካታ ስደተኞች ምልሰት የስጋት ደመናውን አግዝፎታል

አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ

በፌቨን ጌታቸው
Returnees in quarantine at the Civil Service University in Addis Ababa.
UNICEFEthiopia/2020/NahomTesfaye
28 April 2020

የ17 ዓመቱ ብርሃን በርኼ ወደ ውጪ ሃገር ሲሄድ የቤተሰቦቹን የነገ ብሩህ ተስፋ እውን እንደሚያደርግ አስቦ ነበር፡፡ ከሚኖርበት ከኢትዮጵያ ከሰሜን የትግራይ አካባቢ ተነሥቶ የተጓዘው ደግሞ ልክ እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች በጅቡቲ እና በየመን አቋርጦ ወደ ሳውዲ ዐረቢያ ነበር፡፡ ይሁንና በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የመን ላይ ሲያዝ ግን ህልሙ ተጨናገፈ፡፡ [ከእገታ] የመፈቻ ገንዘብ እስኪከፈል ድረስ ሕገ-ወጥ ዝውውር፣ ጠለፋ፣ ብዝበዛ፣ እና ግርፋት የተደገሰበትን የመከራ ጉዞ ከሚጀምሩ ከብዙ ወጣቶች መካከል [ብርሃን] አንዱ ነው፡፡

 

የ17 ዓመቱ ብርሃን በርኼ
በየኒሴፍ ኢትዮጵያ/2012/ ናሆምተስፋዬ
የ17 ዓመቱ ብርሃን በርኼ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘውን መኖሪያን ትቶ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ወደ ወደ ሳውዲ ዐረቢያ ተጓዘ፡፡ በሚያዝያ ከሳውዲ ዐረቢያ ተገድዶ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡

የአምስት ወራት እስራትን ተቋቁሞ ካሳለፈ በኋላ፤ ብርሃን የተጠየቀውን ከእገታ የመፈቻ ገንዘብ ሳይከፍል ነበር አጋቾቹ የለቀቁት፡፡ ወደ ሳዉዲ ዐረቢያ ቢያመራም፤ እዚያ እንደደረሰ በሕግ አስከባሪዎች ተያዘ፡፡ ከአንድ ወር የእስር ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ሲደረግ፤ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመገናኘት እና ሕይወቱን ዳግም ለማቃናት ዕድል እንደተፈጠረለት አምኖ ነበር፡፡ ሆኖም ያሰበው ዕድል እውን የሚሆንበት ጊዜ መራዘሙ አልቀረም፤ ምክንያቱም በኮሮና ሻይረስ ወረርሽኝ የተነሣ፥ ብርሃን እና ሌሎች ከስደት ተመላሾች በመልካም ጤንነት ላይ ስለመገኘታቸው እና በቫይረሱ ስላለመጠቃታቸው ለማረጋገጥ የ14 ቀን አስገዳጅ የለይቶ-ማቆያ ውስጥ መሰንበት ስላለባቸው ነው፡፡ በዚህ ወር ተጨማሪ ተመላሾች እንደሚመጡ  የሚጠበቅ እንደመሆኑ፤ ይህንን ተከትሎም [የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር ስለሚያሻቅብ] የሃገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ታይቶ የማይታወቅ ጫና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።  ይህ ጽሁፍ በሚጻፍበት ወቅት ኢትዮጵያ 88 የኮሮና ሻይረስ ተጠቂዎችን  እና የሦስት ታማሚዎችን ኅልፈት ሪፖርት አስመዝግባለች፡፡

እንደ አብዛኞቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ወጣቶች የብርሃንም ታሪክ ይህን መሰል መከራ የሞላበት ነው፤ ጉዞ ሲጀምሩ ያላወቁት፤ ኋላ ግን በአደጋው መኖሩን ያዩበት ነው፡፡ [ብርሃን] አባቱ በሞት ከተለዩ በኋላ፥ ትምህርቱን ከሦስተኛ ክፍል  አቋርጦ ነበር ቤተሰቡን የመንከባከብ ኃላፊነት በመሸከም ወደ እርሻ የተሠማራው፡፡ 

”ወደ ሳውዲ ዐረቢያ ከሄድኩ፤ እናቴን እና ሦስት እኅት እና ወንድሞቼን መርዳት እንደምችል አምኜ ነበር” የሚለው ብርሃን፤ ዝናቡ ባለመለገሱ እና ሰብሉም እምብዛም ባለመስጠቱ፤ ወደ ደለላ በመሄድ ከሃገር እንደሚያስወጣውን የተስፋ ቃል ተቀበለ፡፡

“[በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች] ስንያዝ፤ በአንድ ጠባብ ክፍል 115ታችንን አጨቁን፡፡ በቀን ሁለት ቁራሽ ዳቦ እና ጉንጭ የማይሞላ  ውሃ ብቻ ነበር የሚሰጡን” ይላል፡፡ “[በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት] ስንያዝ፤ በአንድ ጠባብ ክፍል 115ታችንን አጨቁን፡፡ በቀን ሁለት ቁራሽ ዳቦ እና ጥቂት ውሃ ብቻ ነበር የሚሰጡን” ይላል፡፡

አሁን ወደ ሃገሩ የተመለሰው ብርሃን፤ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት በመቶዎች ከሚቆጠሩት ተመላሾች መካከል አንዱ ነው፡፡ በለይቶ-ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ያሉት የሕክምና ዶክተሮች እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ቁጥራቸው እየናረ የመጣውን ተመላሾች ለማስተናገድ እየታገሉ ይገኛሉ፡፡

ዶክተር ምንያህል ታዬ
በየኒሴፍ ኢትዮጵያ/2012/ ናሆምተስፋዬ
ዶክተር ምንያህል ታዬ፤ አዲስ አበባ በሚገኘው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል፤

“እንደደረሱ እያንዳንዳቸውን ለየብቻ በአንድ ክፍል ውስጥ አስቀምጠን፤ የበሽታው ምልክቶች እና ትኩሳት ያለባቸው ስለመሆኑ እንመረምራቸዋለን” የሚሉት አዲስ አበባ ባለው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተቋቋመው የለይቶ-ማቆያ ማዕከል ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ምንያህል ታዬ ሲሆኑ አክለውም “የበሽታውን ምልክቶች እና ከፍተኛ ትኩሳት ካገኘን፤ ወደተዘጋጀው ለይቶ-ማከሚያ ቦታ አንወስዳቸዋለን፡፡ ከኮቪድ-19 በተጨማሪ፤ ምናልባት በእስር ቆይታቸው ወቅት ያጠቃቸው ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስለመኖሩ ጭምር እንመረምራለን፡፡”

የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛዋ ጥሩሰው ጌታሁን
በየኒሴፍ ኢትዮጵያ/2012/ ናሆምተስፋዬ
የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛዋ ጥሩሰው ጌታሁን፤ አዲስ አበባ በሚገኘው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ከስደት የተመለሰ ወጣት ስትመዘግብ፤ በየኒሴፍ ኢትዮጵያ/2012/ ናሆምተስፋዬ

የስደት ተመላሾች ቁጥር በድንገት ማሻቀብ፤ የአገር ውስጥ አቅምን፤ በተለይም የጤና ሥርዓቱን አቅም እየተፈታተነ ነው፡፡ 434 አሳዳጊ -የሌላቸው [(unaccompanied children)] ሕፃናትን ጨምሮ (ከእነዚህ ውስጥ 135ቱ ሴቶች ልጆች)፤ በድምሩ 3,273 ከስደት ተመላሾችን መንግሥት በአዲስ አበባ በአቋቋማቸው የተለያዩ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ውስጥ ተመዝግበው ተቀምጠዋል፡፡ 

የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ የሆነችው ጥሩሰው ጌታሁን፤ በማዕከሉ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕፃናት የመለየት፣ ገጸ-ታሪካቸውን የማጠናቀር፣ እና የመመዝገብ ተግባር ታከናውናለች፡፡ አሳዳጊ  የሌላቸው ለአካለ-መጠን ያልደረሱ ልጆች ተጋላጭ ስደተኞች ከሚባለው ክፍል የሚመደቡ እንደመሆናቸው የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ገጸ-ታሪካቸውን ከማጠናቀር፣ ከመመዝገብ፣ እና ፍላጎታቸውን ከመለየት ባለፈ፤ የክትትል አገልግሎት የሚሻ በደል እንደደረሰባቸው የሚጠቁሙ ፍንጮች [ወይም ምልክቶች] መኖራቸውን ይመረምራሉ፤ የቤተሰቦቻቸውንም አድራሻ ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ የቤተሰቦቻቸውን አድራሻ የማግኘት ጉዳይ፤ ዝርዝር ምዘና ለማካሄድ፣ ቤተሰብን ለማፈላለግ፣ እና መልሶ ለማገኛኘት ወሳኝ ነው፡፡  ከቤተሰብ ጋር መልሶ ማገናኘት የማይቻል ሲሆን፤ ከማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ወይም ልጆቹ ከመጡበት አካባቢ ከሚንቀሳቀሱት የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር በመተባበር ለልጆቹ ክብካቤ የሚሰጥበትን አማራጮች ያፈላልጋሉ፡፡

የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች የአእምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፎችን የሚሹትን ሕፃናት የመለየት ተግባርም ያከናውናሉ፡፡ ከፊሉ ሕፃናት በደላሎች የሚሰነዘር ዛቻን እና በማቆያ ቤቶች መታሠርን ጨምሮ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞቹ መሠረታዊ የምክር አገልግሎት የሚሰጧቸው ሲሆን፤ ሥር የሰደደ የስነ-ልቦና መታወክ የገጠማቸውን ሕፃናት ደግሞ ወደ ላቀ ልዩ የሕክምና አገልግሎት ይመሯቸዋል፡፡

የተለይቶ ቆይታው ጊዜ እንዳበቃ ሕፃናቱን ከቤተሰቦቻቸው ጋር መልሶ ለማገናኘት ምኞቷ መሆኑን የምትናገረው ጥሩሰው፤ እስከዛው ግን በለይቶ ቆይታው ወቅት ሕፃናቱን ከኮቪድ-19 እንዲጠበቁ ትፈልጋለች፡፡

“ምንም እንኳ [ኮቪድ-19ን የተመለከተ] መረጃ ለሁሉም ተመላሾች የሚሰጥ ቢሆንም፤ ሕፃናት [እና ወጣቶች] ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዴት መከላከል እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ የተለየ አገልግሎት እና ልጅ-ተኮር የሆነ መልእክት ሊሰጣቸው ይገባል”፡፡

“ሕፃናት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እና ከሌላው ሊነጠሉ ይገባል፤ ምክንያቱም ስለ ኮቪድ-19 ሲሰሙ ከሌሎች በበለጠ ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ የሰፋ ነው”፤ ሲል የሚገልጸው ሌላው የማዕከሉ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ የሆነው ጎሹ ብርሃኔ ነው፡፡ “ቤተሰቦቻቸውን አንዴ አፈላልገን ካገኘን፤ እነሱን የመመለስ ሥራ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው” ሲል ያክላል፡፡

ብርሃን በሳውዲ ዐረቢያ ምኞቱ ስላልሠመረ አልተከፋም፡፡

“አደጋውን አይቻለሁ እና ተመልሼ መሄድ አልፈልግም፡፡ ነገር ግን ያው አሁን ወደ ሀገርቤት ተመልሻለሁና ሥራ አግኝቼ ቤተሰቤን ለመርዳት እንድችል እመኛለሁ”፡፡

የዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት (International Organization for Migration) እና ዩኒሴፍ ስድተኞችን በመመዝገብ፣ ተጋላጭ የሆኑትን ይልቁንም ሕፃናትን በመለየት፣ እና ተለይቶ በታወቀው ፍላጎቶቻቸው መሠረት ወደ ተገቢው አገልግሎቶች መምራታቸውን በማረጋገጥ ረገድ መንግሥትን እያገዙ ይገኛሉ፡፡ ሥራው አጃቢ የሌላቸውን ሕፃናት ቤተሰቦችን ማፈላለግን፣ ሕፃናቱ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቤታቸው ስለመመለሳቸው ማረጋገጥን፣ እና ወደ ማኅበረሰቡ ያለችግር እንዲቀላቀሉ ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ ድርጅቶች ለተመላሾቹ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ሳሙና፣ እንዳስፈላጊነቱ ውሃ፣ የመዝናኛ ቁሳቁሶች፣ ድንኳኖች፣ የመኝታ አልባሳት፣ እና ሌሎች አስፈላጊ ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ የዓለም አቀፉ የስደት ድርጅት መንግስት ተጋላጭ ስደተኞችን በዘላቂነት መልሶ ለማቀላቀል የሚያስችለውን እቅድ እንዲቀርጽ እና እንዲተገብር  ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

የእንግሊዙ የዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (Department for International Development) በሰጠው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት፤ ዩኒሴፍ እንደ ብርሃን ላሉ ሕፃናት እና ወጣቶች የሚሰጠውን ጥበቃ ለማሻሻል የሚያስችል ለሁለት ዓመታት የሚቆይ መርኅ-ግብር እየተገበረ ይገኛል፡፡ እቅዱ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞችን ማሠልጠንን፣ ተጋላጭ ሕፃናትን ገና በጠዋቱ/አስቀድሞ መለየትን፣ እንዲሁም የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ማዘጋጀትን  ይጨምራል፡፡