“ኤዲዩኬሽን ካን ኖት ዌይት” በኢትዮጵያ ውስጥ በሁከት ለተጠቁ ሕፃናት ትምህርት የሚቀርብበትን ውጥን ይፋ አደረገ

በሦስት የትግበራ ዓመታት በ165 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አማካኝነት በግጭት ቀጣናዎች ለሚገኙ ለ746 ሺህ ሕፃናት የትምህርት አገልገሎት ይሰጣል

13 February 2020
ECW
UNICEFEthiopia/2020/NahomTesfaye
ECW launch

በድንገተኛ የአደጋ ቀጣናዎች ውስጥ የትምህርት አቅርቦትን በመደገፍ ላይ የሚያተኩረው ዓለም-አቀፉ ፈንድ፤ ማለትም በእንግሊዘኛው አጠራር “ኤዲዩኬሽን ካን ኖት ዌይት - ኢ/ሲ/ደብሊው”፤ በሦስት የትግበራ ዓመታት እና በ165 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ እና በሁከት ለተጠቁ 746 ሺህ ሕፃናት የትምህርት አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ውጥን ይፋ አደረገ፡፡ ጎን ለጎንም፤ መርኀ-ግብሩን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የሚያስፈልገውን 138 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር አሟልቶ ለማሰባሰብ፤ ብሎም በቀዳሚነት የሚከናወኑ ሥራዎችን ለመደገፍ እንዲቻል የ27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወረት/የመነሻ ገንዘብ ለመለገስ ማቀዱን ኢ/ሲ/ደብሊው አስታውቋል፡፡

የኢ/ሲ/ደብሊው ዳይሬክተር ያስሚን ሸሪፍ፤ ውጥኑ በመዲናዋ በአዲስ አበባ ይፋ ሲደረግ እንደተናገሩት፤ መርኀ-ግብሩ በጥቃት፣ በድርቅ፣ በመፈናቀል፣ እና በሌሎች ሁከቶች በተጎዱ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት እና ወጣቶች ትምህርት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ዓይነተኛ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የተቀረጸ ነው፡፡

“ከመንግሥት እና ከሁሉም አጋሮቻችን ጋር ከሁሉም የኢ/ሲ/ደብሊው አጋሮችን ጋር አብሮ በመሥራት፤ ይህ ውህሎተ-ንዋይ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እየኖሩ ላሉ ልጃገረዶች እና ወንድ ልጆች የደኅንነት ከለላ የተጎናጸፈ የመማሪያ ከባቢን እና ጥራት ያለው የትምህርት አገልግሎትን ለማቅረብ ያስችላል” ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ “ወደኋላ ትተናቸው ሊቀሩ አይገባም፡፡ እነሱም የማደግ እና የመመንደግ መብት አላቸው፡፡ አጅግ ብዙ የሚያሳኩት እና የሚያበረክቱት ነገሮች አሏቸው፡፡ የሚፈለገውን ሁሉንም ሐብት ለማሟላት አብሮ በመሥራት፤ በኢትዮጵያ አንድም ሕፃን እንኳ ሳይካተት አለመቅረቱን ለማረጋገጥ አሁን ዕድሉ አለን” ሲሉ አክለዋል፡፡

በኢ/ሲ/ደብሊው እና በልዩ ልዩ አጋሮች (ማለትም የተባበሩት መንግሥታት የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች፣ የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች፣ እና ለጋሾች) ደጋፊነት በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ይህ የብዝኀ-ዓመት የመልሶ-ማገገሚያ መርኀ-ግብር፤ የተፈናቃይ ሕፃናትን የትምህርት ፍላጎቶች መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 1.4 ሚሊዮን ተፈናቃይ፣ ከስደት ተመላሽ፣ እና ሰደተኛ ሕፃናት ያላት ሲሆን፤ የአብዛኞቹም መንሥኤ ግጭት እና የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮኑ ሕፃናት ከትምህርት ቤት ውጪ ሲሆኑ፤ 527 ሺዎቹ ደግሞ ልጃገረዶች ናቸው፡፡ የቅርብ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ 728 ትምህርት ቤቶች በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሣ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የኢ/ሲ/ደብሊው መርኀ-ግብር ለ746 ሺህ ሕፃናት (74 ሺህ 600 የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ጨምሮ፤ 380 ሺህ ወንድ ልጆች እና 365 ልጃገረዶች) የመማር ዕድልን የሚያቋድስ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል፤ 213 ሺዎቹ ሕፃናት የመዋዕለ-ሕፃናት ትምህርትን የሚያገኙ ሲሆን፤ 532 ሺዎቹ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም መርኀ-ግብሩ ስደተኞችን የሚያስተምሩ 1 ሺህ 200 መምህሮችን በዲፕሎማ ደረጃ በማብቃት አቅማቸውን ይበልጥ ይገነባል፡፡

በዐማራ፣ በኦሮሚያ፣ እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ እየኖሩ ላሉ የ60 ሺህ 478 ተፈናቃይ ሕፃናት፣ ተመላሾች፣ እና የተቀባይ ማኅበረሰቦቹ ሕፃናት የትምህርት ፍላጎቶችን ምላሽ ለመስጠት፤ ኢ/ሲ/ደብሊው እንደ ወረት/የመነሻ ገንዘብ ሆኖ የሚያገለግል 27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድቧል፡፡ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ ከፊሉ፤ መርኀ-ግብሩን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የጎደለውን 138 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ይውላል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር፤ ከሴቭ ዘ ቺልድረን ኢንተርናሽናል፣ ከዩኒሴፍ፣ ከኢ/ሲ/ደብሊው፣ እና ኤዲዩኬሽን ክላስተር ጋር በመተባበር መርኀ-ግብሩን ይመራል፡፡ ዩኒሴፍ እና ሴቭ ዘ ቺልድረን ደግሞ፤ ኢ/ሲ/ደብሊው ለመስጠት ያቀደውን እና ለሦስት ዓመታት የሚካሄደውን የ27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የልገሳ ገንዘብ ወደ ትግበራ ያስገባሉ፡፡

 

Media Contacts

Wossen Mulatu

Communication Officer

UNICEF Ethiopia

Tel: +251 115 184028

Hiwot Emishaw

Save The Children

Tel: +251 911 124996

ስለ ኤዲዩኬሽን ካን ኖት ዌይት (ኢ/ሲ/ደብሊው)፡

ኢ/ሲ/ደብሊው በድንገተኛ የአደጋ ሁኔታዎች ውስጥ የትምህርት አገልግሎትን በማቅረብ ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ዓለም-አቀፍ ፈንድ ነው፡፡ ኢ/ሲ/ደብሊው በግጭት እና በሁከት ድባቦች ውስጥ የሚገኙ የ75 ሚሊዮን ሕፃናትን እና ወጣቶችን አጣዳፊ የትምህርት ፍላጎቶች ለመመለስ፤ የመንግሥት እና የግል ለጋሾችን ጨምሮ፤ በዓለም-አቀፍ የሰብአዊ እና የልማት ተራድኦ ተዋናዮች የተመሠረተ ነው፡፡ የኢ/ሲ/ደብሊው ውህሎተ-ንዋይ የሚያፈስበት አሠራር የተነደፈው፤ በመሬት ላይ በተጨባጭ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ተዋናዮች ይበልጥ የሚደጋገፉበትን አግባብ የሚያበረታታ ሁኔታን ለመፍጠር ሲሆን፤ ይህም የረድኤት እና የልማት ድርጅቶች የጥረታቸው ውጤት በትምህርት ዘርፍ እንዲታይ የአቅም ቅንጅት መፍጠራቸውን በሚያረጋግጥ አኳኋን ነው፡፡ ኢ/ሲ/ደብሊው በዩኒሴፍ ጥላ ሥር የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ ፈንዱ የሚተዳደረው በዩኒሴፍ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል፣ እና የአስተዳደራዊ ሕግጋት እና ደንቦች ሆኖ፤ የክዋኔ ሥራዎች የሚመሩት ደግሞ ራሱን በቻለ በፈንዱ የአስተዳደር መዋቅር ነው፡፡

 

ኢ/ሲ/ደብሊው እስከአሁን ድረስ ያደረገው ውህሎተ-ንዋይ፤ በትጥቅ ግጭት፣ ድንገተኛ አደጋዎች፣ እና አስገዳጅ መፈናቀሎች የተጠቁ 30 ሃገራትን ያዳረሰ ነው፡፡

 

እባክዎ በትዊተር ይከተሉን፡ @EduCannotWait  @YasmineSherif1   @KentPage  

 

ለተጨማሪ መረጃ የሚከተሉትን ድረ-ገጾች ይጎብኙ፡ www.educationcannotwait.org እና www.act4education.org